ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ እንግዶች ደኅንነቱ የተረጋገጠ መስተንግዶ ለማድረግ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ላይ ቅንጅታዊ አመራር ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ገለጸ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ በይፋ ስራ በመጀመረበት መድረክ ላይ በቅርቡ የሚደረገው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ደኅንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መስክ ቅንጅት እና ርብርብ በማድረግ ውጤታማ አመራር ለመስጠት አቅጣጫ ተቀምጧል።
የአቪዬሽን ዘርፍ የሴኪዩሪቲ ሥራና ዝግጁነት ሁሌም በንቃት የሚተገበር ቢሆንም ከ12 ዓመት በኋላ በሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ለሚደረግው ሀገራዊ ኦዲት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለሚያደርገው ኦዲት ሁሉም የኮሚቴው አባል ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ለማድረግ የድርሻ ተግባራትን በመውሰድ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተመልክቷል።
የኮሚቴ ሰብሳቢና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሲሳይ ቶላ በመክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸው አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኤርፖርቶች አገልግሎትና የአየር ክልል ቁጥጥር በሚመለከት በቅርቡ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በካናዳ እና እስራኤልን ጨምሮ በሌሎች 10 ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲቶችን ያለ ምንም ግኝት ማለፍ መቻሉን አመልክተዋል።
ቢሆንም በየጊዜው ተለዋዋጭ በሆነው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ውስጥ የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ሥራውን በይፋ መጀመሩ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እና ውሳኔዎችን ለመስጠት እንዲሁም ቅንጅታዊ አመራር ለመዘርጋት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ከመቋቋሙ አስቀድሞ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሪነት በአቪዬሽን ዘርፉ ተግባራዊ በተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ለውጥ በመከናወኑ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አቶ ሲሳይ አመላክተዋል፡፡
በእነዚህ የሪፎርም ስራዎችም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 230 ኪ.ግ የአደንዛዥ ዕፅ ፣ በኢትዮጵያ የምንዛሬ ዋጋ ሲተመን 95 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የተለያዩ ሀገራት ሕገ-ወጥ ገንዘብ እንዲሁም 125 ድሮን፣ 428 ባይነኩላር እና ሌሎችም ለታጣቂዎች የሚውሉ የቴክኖሎጂና የስለላ መሳሪያዎች መያዝ መቻሉን ገልጸዋል።
የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እንደ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ ፌዴራል ፖሊስን ፤ ውጭጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮችን ጨምሮ 10 ተቋማትን በአባልነት ያካተተ ኮሚቴ ነው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት የላከልን መረጃ ለግማሽ ቀን የተካሄደው የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ስብሰባ የኮሚቴውን መተዳደሪያ መመሪያ በማጽደቅና የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁን አመልክቷል።