ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸው ተገለጸ
ከየካቲት 6 እስከ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚሰጠው ፈተና ከ112 ሺህ በላይ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎች ምዝገባ ማድረጋቸውን በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ ሰዒድ መሃመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የፈተና ጥያቄዎች ፣ የኮምፒውተር ፣ ፈተና የሚሰጥባቸው የትምህርት መስኮች ልየታን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለፁት።
ፈተናው መቀሌ አክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥም ነው የገለጹት ።
አክለውም ፥ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ቢያጋጥም ችግር እንዳይፈጠር በሁሉም የፈተና ማስጫ ማዕከላት ጄነሬተር ዝግጁ መደረጉንም አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት በፈተና አሰጣጥ ሂደትያጋጠሙ ችግሮች ዘንድሮ እንዳይደገሙ በቂ ዝግጅት መደረጉን አቶ ሰኢድ ተናግረዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ