የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ እጩ መኮንኖችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ለ24ኛ ዙር በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የአንድነት ኮርስ እጩ መኮንኖችን አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ጀኔራል መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ተመራቂ መኮንኖች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በ117 ዓመት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ታሪክ መኮንኖች ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈሉት ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ኃላፊ ሌ/ጄ ይመር መኮንን በበኩላቸው÷ ሠራዊቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የአካዳሚው ሚና ትልቅ ነው፤ በቀጣይም አስተዋጽኦው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በእውቀት፣ በክኅሎት እና በአስተሳሰብ ሙሉ የሚያደርጋቸውን የመሪነት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂ መኮንኖች አረጋግጠዋል።
ለተመራቂዎች ማዕረግ የማልበስ ሥነ-ሥርዓትም የተከናወነ ሲሆን÷ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ መኮንኖችም የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ