በጣሊያን ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ሰርከስ ቡድን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ተመዘገበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣሊያን በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው የብላክ ላየን ሰርከስ ቡድን የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ተመዝግቧል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ÷ የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ላደረጉት ብላክ ላየን የሰርከስ ቡድን አባላት አቀባበል አድርገዋል፡፡
አቶ ቀጄላ የሰርከስ ቡድኑ ባስመዘገበው ድል የተሠማቸውን ደስታ ገልፀው÷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም ማስተላለፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰርከስ ማኅበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ተክሉ አሻግር በበኩላቸው÷ ውጤቱ የመጀመሪያ አለመሆኑን በመግለጽ ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያውያን የዓለምን ክብረ ወሰን እንደሰበሩ አስታውሰዋል፡፡
በዘርፉ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በከፍተኛ ሁኔታ እንድትታወቅ ጠንክረው እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡
እንዲሁም በፈረንሳይ ሞንተካርሎ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል የተሳተፈው አፍርካን ድሪም የሰርከስ ቡድን የብር ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት በማግኘት በድል መመለሱ ተመላክቷል፡፡