ጥቂት ስለቲቢ በሽታ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቲቢ በሽታ መንስኤው ረቂቅ በሆነው “ማይኮባክቴሪያም ቲዩበርክሎስስ” የተባለ ባክቴሪያ ነው፡፡
ቲቢ ዕድሜን፣ ፆታን፣ ዘርንና ቀለምን ሳይለይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ተላላፊ በሽታ ቢሆንም በበሽታው በበለጠ የሚጠቁት በአምራች ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና የቤተሰብ ኃላፊ የሆኑ ዜጎች እንደሆኑ ይነሳል፡፡
በተያያዘም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የሰውነት መከለከያ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ለምሳሌ ኤችአይቪ፣ የካንሠር እና የስኳር ሕሙማን፣ የምግብ እጥረት ያለባቸው፣ በአክታ ምርመራ ቲቢ እንዳለባቸው ከተረጋገጠ ሕሙማን ጋር አብረው የሚኖሩ እንዲሁም በተጨናነቁና በተፋፈጉ ቦታዎች የሚኖሩ/የሚሠሩ/የሚሰባበሱ ሰዎች እንዲሁም የአልኮንና የትምባሆ ሱሰኞች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡
የቲቢ በሽታ እንዴት ይተላለፋል?
ቲቢ የሚተላለፈው በአብዛኛው በትንፋሽ አማካኝነት ሲሆን፥ ይኸውም አንድ በሳንባ ቲቢ የተያዘ ሕመምተኛ በሚስልበት፣ በሚያስነጥስበት፣ በሚተፋበት፣ ወይም በሚናገርበት ወዘተ ወቅት የቲቢ በሽታ አምጪ ባክቴሪያን የያዙ የአክታ ብናኞች ወደ አየር ስለሚረጩና ብናኞችም በአቅራቢያው ያሉ ሰዎች አየር ወደ ውስጥ በሚተነፍሱበት ጊዜ በቀላሉ ወደ ሳንባው ውስጥ ገብተው ለማጥቃት ዕድል ስለሚያገኙ ነው፡፡
ቲቢ “ማይኮባክቴሪያም ቦቪስ” በተባለ ባክቴሪያ የተጠቁ የቤት እንስሳት ወተት ሳይፈላ ቢጠጣ ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችልም መረጋገጡን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቲቢ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የቲቢ በሽታ 80 ከመቶ የሚያጠቃው ሳንባን በመሆኑ የሳንባ ቲቢ በሽታ ዋናው ምልክት ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የዘለቀ ሳል ነው፡፡
ሳሉ አክታ ያለውና ደም የቀላቀለ ወይም ያልቀላቀለ ወይም ደረቅ ሊሆን የሚችል ሲሆን፥ ሕመምተኛው ከሳሉ በተጨማሪ በደረቱ አካባቢ የውጋት ስሜት፣ መጠነኛ የሆነ ትኩሳት፣ ሌሊት በመኝታ ጊዜ ማላብ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሰውነት መድከም የመሳሰሉ አጠቃላይ የሆኑ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
የበሽታው ምልክት እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ዓይነት እንደሚለያይም ይነሳል፡፡
የቲቢ በሽታን ማዳን ይቻላል?
ቲቢ መድኃኒት ስላለው በአግባቡ ከታከሙት የሚድን በሽታ ነው፡፡ የበሽታው ምርመራም ሆነ ሕክምና በመንግሥታዊና ሕክምናውን እንዲሰጡ በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነፃ ማግኘት ስለሚቻል ማንኛውም ሰው የበሽታው ምልክቶች ሲታዩበት አገልግሎቱን ወደሚሰጥ ጤና ተቋማት መሄድ እንደሚኖርበት ይመከራል፡፡
ሆኖም የቲቢ መድኃኒት በታዘዘው መጠንና ጊዜ ባይወሰድ ችግር ስለሚያስከትል ሕመምተኛው የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ በየቀኑ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡
ሕክምናው ከተቋረጠ ግን የበሽታ መንስኤ የሆነው ባክቴሪያ የፀረ-ቲቢን መድኃኒቶችን በመላመድ በመደበኛው የቲቢ ሕክምና ዘዴ መዳን የማይችል የቲቢ ዓይነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ምንድን ነው?
መድኃኒትን የተላመደ ቲቢ በሽታ መድኃኒት ያልተላመደ ቲቢን ለማከም የሚያገለግሉ መድኃኒቶችን የተላመደ የቲቢ በሽታ ዓይነት ነው፡፡
በሽታው የሚከሰተው ታካሚዎች መድኃኒቶችን በታዘዘው መሠረት ካላመውሰድና የክትትል ጉድለት ቢሆንም በሽታው መድኃኒት እንዳልተላመደው ቲቢ ሁሉ በትንፋሽ አማካይነትም ይተላለፋል፡፡
መድኃኒት ያልተላመደውም ሆነ መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ዓይነቶች መንስኤያቸው፣ መተላለፊያ መንገዶቻቸውና ምልክቶቻቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም መድኃኒትን ለተላመደ ቲቢ ሕክምና የሚሰጡ መድኃኒቶች ዓይነትና ብዛት እንዲሁም ሕክምናው የሚፈጅበት ጊዜ ይለያል፡፡
ይሁን እንጂ መድኃኒትን የተላመደው ቲቢም በአግባቡ ከታከሙት መዳን ይችላል፡፡
የቲቢ በሽታን መከላከል ይቻላል?
መድኃኒት ያልተላመደውንም ሆነ መድኃኒት የተላመደ ቲቢን መከላከል የሚቻል ሲሆን፥ የቲቢ ሕሙማን፣ ቤተሰቦቻቸውና በአጠቃላይ ሕብረተሰቡ የግልና የጋራ ኃላፊነታቸውንና ድርሻቸውን በታማኝነት ቢወጡ በሽታውን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እንደሚፋጠን ይታመናል፡፡