ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የተሳተፉበት የፈረስ ጉግስ ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የተሳተፉበት ዓመታዊ የፈረስ ጉግስ ውድድርና ትርኢት መርሐ ግብር በሰንዳፋ በኬ ተካሄደ።
ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የባህል ቡድኖችም የተሳተፉበት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ እንደገለጹት፥ በኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ክዋኔ ውስጥ ፈረስ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
በዛሬው እለት በሰንዳፋ በኬ በተካሄደው የፈረስ ጉግስ ውድድርና ትርኢት ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፥ ሁነቱ ጥልቅ እሴቶች የተንጸባረቁበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከውድድሩ በተጓዳኝ የባህል ምግቦች፣ አልባሳት፣ የባህላዊ ቁሳቁሶችና ሌሎችም ሃብቶች ለእይታ የቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት በርካቶችን ባሳተፈና ባማረ መልኩ በየዓመቱ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው፥ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዝናሽ አበቤ እንደገለጹት፥ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው።
በተለያዩ ባህላዊ ኹነትና የአስተዳደር ሥርዓት አብሮ የኖረ እና ታሪካዊ ትስስርም ጭምር እንዳለው አንስተዋል።
በመሆኑም የፈረስ ውድድሩ ካለው ባህላዊ እሴት፣ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር በቀጣይ የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በዛሬው እለት በውድድሩ ለተሳተፉ ፈረሰኞች የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለአሸናፊዎች የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን የዘገበው ኢዜአ ነው።