መንግስት በውስጥና በውጭ የተቃጣበትን የተቀናጀ ዘመቻ እየመከተ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በውስጥ እና በውጭ የተቃጣበትን የተቀናጀ ዘመቻ እየመከተ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የቤኒሸንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር “ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ የህዝብ ውይይት መድረክ ተካሄዷል።
አቶ አሻድሌ በውይይቱ÷ በአማራ ክልል የተፈጠረው ቀውስ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ከፅንፈኛ ሀይሎች ጋር በመተባበር የፈጠሩት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ጠንካራ ህዝብና መንግስት ያላት በመሆኑ የተቃጣው የውስጥና የውጭ የተቀናጀ ዘመቻ እየተመከተ ይገኛል ብለዋል።
ፅንፈኛው ቡድን ህዝብን ለመከፋፈል እያደረገ ያለውን ዘመቻ የአዊ ህዝብ በአንድነት በመቆም ሊመክተው እንደሚገባ እንዲሁም ከመላከያ ሀይሉ ጋር በመቆም የአካባቢውን ሰላም ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የህዝቡ ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብና በስክነት ታይተው የሚፈቱ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ ጥያቄዎችን በሀይል ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ ግን የሚወሰደው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያውያን ከአብሮነት ውጭ ሌላ ምርጫ የሌለን በመሆኑ አብረን በመቆም በጋራ እድገትን ማምጣት ይጠብቅብናል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ መሪን በማክበርና ከመሪ ጋር በመነጋገር የጋራ መፍትሄ ለማምጣት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።