Fana: At a Speed of Life!

ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ መሳሪያውን አስቀምጦ የሃሳብ ንግግር ማድረግ አለበት – አቶ ተስፋዬ በልጂጌ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገር እና ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ መሳሪያውን አስቀምጦ የሃሳብ ንግግር ማድረግ አለበት ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ገለጹ፡፡

በአማራ ክልል 15 ከተሞች የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የመሯቸው የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።

“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በባሕር ዳር ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ሕዝባዊ ውይይቱን የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው መርተውታል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝቡንና ክልሉን ከከፋ ችግር ታድጓል፤ ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ ጎን ቆሞ ለከፈለው መስዋዕትነት ክብርና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

መከላከያ ሠራዊት በሕዝቡ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ ከፍተኛ የሆነ የጥላቻ ዘመቻ ቢከፈትበትም ሕዝቡ የሃሰተኞችን ወሬ ወደ ኋላ በመተውና ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለሰላም ሲሠራ መቆየቱ የአርቆ አሳቢነት ምልክት ነው ሲሉም ነው ያብራሩት።

ሚኒስትሩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያም ሰጥተዋል።

ከክልሉ ውጭ ከሚኖሩ አማራዎች ደኅንነት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ጥያቄ መንግሥት በሚገባ እንደሚገነዘብም ነው የተናገሩት።

የአማራ ሕዝብ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በሰላም እንዲኖር ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከወሰን እና ማንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችም ሕግ እና ሥርዓትን ባማከለ እንዲሁም ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ በዘላቂነት እንዲፈቱ መንግሥት በትኩረት እየሠራበት ነው፤ በተግባርም የተከናወኑ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ “የአማራን ሕዝብ ፍላጎት የማይገነዘብ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሊሆን አይችልም” ሲሉም መልሰዋል።

ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሚወክል እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለማሻሻል በመንግሥት በኩል እንደሚሠራም ነው የጠቆሙት።

አንድ ከሚያደርጉ ይልቅ የቆየ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እሕትማማችነትን የሚንዱ ትርክቶች መገንባታቸው ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብም በተዛቡ ትርክቶች ሰበብ ከባድ ዋጋ እየከፈለ ስለመኾኑ መንግሥትም በውል ተረድቶታል ነው ያሉት።

ይህ እንዲፈታ ሁላችንንም የሚጠቅም፣ በአንድነት ላይ የተመሠረተ፤ እንደ ሀገር ያቆመንን ትክክለኛ የጋራ ታሪካችንን የቃኘ እና በአንድነት የሚያኖረንን ትርክት አጥብቆ መያዝ ይገባል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት ለተነሳው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “ከአፈ ሙዝ የሚገኝ አንዳች ሰላም የለም” ብለዋል።

የጦርነት አሸናፊ እንደሌለ የሚያውቀው መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ እንደሆነም አረጋግጠው፤ መንግሥት የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ እንደድክመትና ተሸናፊነት የሚቆጥሩ አካላት ሕዝብን ለከፋ ጦርነት ሲቀሰቅሱ መስተዋሉን ተናግረዋል።

መንግሥት ግጭት እንዳይቆም የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን በተረዳ ጊዜ ከሕዝብ ጋር በመሆን ሕግን ማስከበሩ የማይቀር ነገር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ለሀገር እና ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ መሳሪያውን አስቀምጦ የሃሳብ ንግግር ማድረግ አለበት፤ ያኔ የመደማመጥ ጊዜ ይመጣል፤ ጥያቄዎችም ይፈታሉ፤ ሰላምም ይሰፍናል ብለዋል።

ሰላም ወዳድ የሆነው የአማራ ሕዝብ እና አመራሮቹ በክልሉ የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ነው የገለጹት።

አስተዋዩ የአማራ ሕዝብ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪክ ነው ያለው፤ አሁንም ቢሆን ነገሮችን ሰክኖ በማየት ክልሉ ሰላም እንዲሆን መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.