Fana: At a Speed of Life!

ህዝብ ለናፈቀዉ ሰላም እዉን መሆን የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝብ ለናፈቀዉ ሰላም እዉን መሆን የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚኮሚቴ አባልና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በክልላዊ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገው የውይይት መድረክ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የደብረታቦር ከተማና የደቡብ ጎንደር ዞን ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ እንዲመለስ አለመደረጉ፣ የልዩ ሀይል መልሶ ማደራጀቱ ላይ የተዛባ መረጃ ለህዝብ እንዲደርስ መደረጉ፣ የተሳሳቱ ትርክቶች ማከም አለመቻሉ፣ የኑሮ ውድነቱ አለመረጋጋት፣ ህገ መንግስቱ አለመሻሻሉ፣ የህዝብ መፈናቀል ማስቆም አለመቻሉ፣ ሚዲያዎች በአግባቡ አለመመራታቸው፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያራርቁ  ሃይሎች እና አብሮ የኖሩ ህዝቦችን ለመለያየት ሃይማኖትን ተገን አድርገው በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ባለመወሰዱ ለሰላም እጦቱ መነሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ ብልፅግና ፓርቲ ያጋጠሙ የሰላም ችግሮችን ስረ መሰረት ለመለየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ የሚያስችል ግምገማ በቅርቡ ማካሄዱን አስታውሰው፤ በተለይ የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እና ክልሉ ወደመደበኛው እንቅስቀሴ እንዲመለስ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ፓርቲው አቅጣጫ መስቀመጡን ገልጸዋል።

በሰላምና በልማት ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሀገር ለመገንባት የጋራ መግባባቶች፣ ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመጣ ምንጮችን ለማዳመጥ የውይይት መድረኩ አስፈላጊነቱን ገልፀዋል።

የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ህጋዊነት ተከትሎ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ አሕመድ፤ በእኩልነት አንድነቷ የዳበረ በመከባባበር የተመሰረተ ወንድማማችነት የጋራ ትርክት መንገንባት ላይ ስራ ይቀረናል ብለዋል።

ብልጽግና የህዝቦችን ጥቅም ለማስከበር የተመሰረተ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ አሕመድ፤ ለፓርቲ መወለድ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን ታሪክ ሰርቷል ሲሉ ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነቱን መቆጣጣርን ጨምሮ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአማራ ህዝብ የኢትዮጵያ መሰረት ነው፤ በሀገር የመጣን ጥፋት ለመመለስ ኢትዮጵያን ያፀና ነው፤ የአማራ ህዝብ ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ አካላትን ትግል ማድረግ ያስፈልጋል የእርስ በእርስ መጠፋፋት ይበቃናል ብለዋል፡፡

የእኔ ሃሳብ ብቻ ነዉ ትክክል የሚል አስተሳሰብ ለማንም የማይበጅ መሆኑን በመግለጽ፤ ህዝብ ለናፈቀዉ ሰላም እዉን መሆን የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ለስኬቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻችንም አብረን መቆም አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

ለዘመናት እየታዩ ያሉ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆሙም መንግስትና ህዝብ በጋራ መስራትና በሰላማዊ መንገድ  ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ መስራት ይገባል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ክፋት የሚያስቡ የውጪ እና የውስጥ ኃይሎች ወደ ጦርነት እንድንገባና በዚህም የአማራ ህዝብ ለከፍተኛ ስቃይ እንዲዳረግ ሆኗል ያሉት አቶ ርስቱ፤ የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ፣ በሰላም አክባሪነቱ፣ የሚታወቅ በሰላም በፍቅር እንዲኖር የሚሰብክ ህዝብ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ባልተገባ መንገድ የሚሄዱ ሃይሎች ሌላው አካባቢ ወደ ልማት ሲመለስ የአማራ ክልል ወደ ልማቱ እንዳይመጣ ማድረጋቸዉን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.