የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መወያየትና መመካከርን ቀዳሚ ልናደርገዉ ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መወያየትና መመካከርን ቀዳሚ ልናደርገዉ ይገባል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ከወልዲያ ከተማና ከሰሜን ወሎ ዞን ከተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በሰላምና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
“ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በተደረገዉ ምክክር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ፣ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሥራ ሀላፊዎች እና የኅብረተሰቡ ተወካዮች ተገኝተዋል።
አቶ ጥላሁን ከበደ በመድረኩ፤ እርስ በርስ እያጋደሉን፣ ታሪክን እንዲበላሽ እየሰሩ ያሉ ፅንፈኛ ሀይሎች የአማራ ህዝብ ጠላት ናቸው ብለዋል።
የአማራ ህዝብን ያደሩ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት መንግስት ህግን እና አሰራር ተከትሎ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ የተጀመሩት የልማት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ጥላሁን፤ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መወያየትን፣ መመካከርን፣ ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳ ልናደርገዉ ይገባል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸዉ ብልጽግና ፓርቲ ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ ለማስቀመጥና ሕዝባዊ አንድነት ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮችን በቅርብ ጊዜ ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ አቅደዉ እየሰሩ ያሉ ፅንፈኛ ቡድኖችን ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት መታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ ሁለንታናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ሕዝቡ የሚያነሳቸው አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ፣ የዋሉና ያደሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ህዝቡም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመስራት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።