ለእኩይ አላማ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ህዝቡ ማገዝ አለበት – አቶ ኦርዲን
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለእኩይ አላማ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ህዝቡ ማገዝ አለበት ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን ገለጹ።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ “ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሠላምና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ጨምሮ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ፣ የብልፅግና ፓርቲ አፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሃጂ ኢሴ አደም፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ አሊ እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በከሚሴና አካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በመድረኩም የአማራ ክልል አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስስ መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከተሳታፊዎቹም አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
የሰላም ጉዳይ በጋራ የምንሰራበት የጋራ አጀንዳችን ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ለግጭትና አለመረጋጋት የሚጥሩ አካላትን በፅኑ እንታገላለን እናወግዛለንም ነው ያሉት።
በዞኑ በተፈጠረው ሰላም የግብርና፣ የትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችና የልማት ስራዎች በጥሩ ሁኔታ መቀጠላቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ለዚህም የጸጥታ አካላት በተለይም የመከላከያ ሰራዊት የላቀ ሚና፣ የህብረተሰቡ ትብብርና ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ታክሎበት ነው ብለዋል።
በቀጣይም ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የፅንፈኞችን አፍራሽ እንቅስቃሴ በመታገል የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ የዞኑ ህዝብ አብሮነቱን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በቀጣይም ለእኩይ አላማ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል ከዞኑ ባለፈ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ መጠየቃቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመልክቷል።