የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የላቀ የምርምር ተቋም ለመሆን በትጋት መሥራት አለባቸው -ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የላቀ የምርምር ተቋም ለመሆን በትጋት መሥራት አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጀርመን መንግሥትና በጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች አዘጋጅነት ለአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ዲን እና አመራሮች የሚሰጠው 9ኛ ዙር ሥልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያ፣ የዩጋንዳ፣ የጋና፣ የታንዛንያ እና የናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲዎች ታድመዋል።
መርሐ ግብሩ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን÷ መስፈርቶችን በማሟላት ጥያቄ በማቅረብ በውድድር የተለዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሆነዋል።
ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችን አቅም ለማጎልበት መሆኑን ገልፀዋል።
በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በእውቀት ሽግግር ዓለም አቀፍ ተፅዕኖን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የላቀ የምርምር ተቋም ለመሆን በትጋት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።
የአሁኑ መድረክም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ መሪዎችና ዲኖች የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የሚያደርጉበት መሆኑን ገልፀዋል።
በጀርመን የኦስናብሩክ ዩኒቨርሲቲ ፒተር ማዬር( ፕ/ር)÷ መድረኩ በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎችን የአመራርነት ብቃትና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው መድረክም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማየት ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል ይሆናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡