ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ድርቅን ተከትሎ የሚመጣን ፈተና ለመመከት የሚያስችል ልማት መሰራቱን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ድርቅን ተከትሎ የሚመጣን ፈተና ለመመከት በ2016 በጀት ዓመት ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱንና ከዚህም ከ120 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከድርቅ መከሰት ጋር በተገናኘ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታትና ከዚያም በፊት በየአሥር ዓመቱ በሀገሪቱ የሚከሰት ድርቅ እንደነበርና አሁንም እንዳለ አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም በየአሥር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ላይ በየሦስት ዓመቱ መከሰት መጀመሩንም ነው ያነሱት፡፡
እንደ ሀገር በነበረው የቆየ ችግር ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጨምሮ ችግሩን የበለጠ እንዳያባብስ መንግስት ምርታማነት ላይ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱንና ከዚህም ከ120 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እንደ አማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ ስለመኖሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት በ1977 ዓ.ም ከነበረው የከፋ ድርቅ ተከስቷል በዚህም ብዙዎች ህይወታቸው እያለፈ ነው የሚለው ፍጹም የተሳሳተ አተያይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰዎች ህይወታቸው ያለፈው በድርቁ ምክንያት ሳይሆን ዓይነተ ልዩ ወባ በመከሰቱ እንደሆነና ይህንንም ለመከላከል መንግስት እየሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ሥራዎች ሲሰሩ እያወገዙ ችግር ሲነሳ ያንን አጋነው እያቀረቡ የሚመጣ ለውጥ ባለመኖሩ የሚያዋጣው ነገር ጠንክሮ መሥራት በመሆኑ ተባብሮ መስራትና ከችግር መላቀቅ ላይ መረባረብ ይሻላል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!