አዲሱ የዓባይ ድልድይ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ ተደርጎበታል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህርዳር ከተማ ለተገነባውአዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደጠቀሱት፤ በአማራ ክልል ባለፉት አምስት አመታት የዓባይ ድልድይን ጨምሮ የክልሉን ልማት ለማፋጠን የሚረዱ በርካታ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም በክልሉ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ የተጀመረ ሲሆን ፥ ከዚህም ውስጥ 1 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ያህሉ ተጠናቆ ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአማካይ 50 ሜትር ስፋት ያለው በሁለት ረድፍ በእያንዳንዳቸው ሶስት መኪና የሚያሳልፍ፣ ሰፊ የሳይክልና የእግረኛ ቦታ ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪና ጥራት የተሰራ የመጀመሪያው ድልድይ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ለፕሮጀክቱም 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ በጥራት በአስፓልት ኮንክሪት የተሰራ መሆኑንና በጥንቃቄ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ በሚችል መልኩ መገንባቱንም አንስተዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው