ችግሮች የሚፈቱት በውይይት ብቻ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ችግሮች የሚፈቱት በውይይት ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም፤ ጠመንጃ ታጥቆ የራስን ህዝብ እያሰቃዩ እታገልልሃለሁ ማለት ትርጉም የሌለው አካሄድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሸኔ በኦሮሚያ ክልል እያደረገ ያለው ይህንኑ እንደሆነ ገልጸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም፣ በዴሞክራሲና በምርጫ ካልሆነ ጠመንጃ ይዞ ወደ ስልጣን መምጣት ፈጽሞ አይቻልም ብለዋል።
ሰላም ሁሌም በውድ ዋጋ የሚገኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 50 ዓመታት ሃሳብን አደራጅቶ የፖለቲካ ፍላጎትን ከማሳካት ይልቅ ጠመንጃን አማራጭ የማድረጉ ልምምድ ለሰላም እንቅፋት መፍጠሩን አብራርተዋል።
ወንድም ወንድሙን ገድሎ ምን አሳካ ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም የሚለው ይሆናል በማለት ገልጸው፤ ችግሮች የሚፈቱት በውይይት ብቻ ነው ብለዋል፡፡