Fana: At a Speed of Life!

በትናንትናው ስንፋጅ ነገን እያጣን ስለሆነ አሰባሳቢ የጋራ ትርክት ያስፈልገናል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በትናንትናው ስንፋጅ ነገን እያጣን ስለሆነ ልክ እንደ ዓድዋ አሰባሳቢ የጋራ ትርክት ያስፈልገናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ ኢትዮጵያ ውስጥ በትናንትናው ስንፋጅ ነገን እያጣን በመሆኑ የጋራ ትርክት እጅግ አስፈላጊና መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ሰው ከትናንት ተምሮ፤ ዛሬ ሠርቶ፤ ነገን ማነጽ እንጂ ዛሬ ላይ ሆኖ በትናንትና እየተፋጀ ነገን ማጣት አይገባውም ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ልክ እንደ ዓድዋ አሰባሳቢ የጋራ ትርክት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ዓድዋ መደመርን በተግባር ያሳየ፤ የጋራ ትርክትን በአንድ ቦታ ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ልክ እንደዚህ ንግግሮቻችንም ሰብሳቢ ቢሆኑ ይመረጣል፤ የሚያዋጣውም ይሄው ነው ብለዋል፡፡

የጋራ ትርክትን በተደራጀ አግባብ ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው የባሰ አደጋ አጋጥሟቸው የነበሩት ደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመን፣ ካናዳ እና ሩዋንዳ ችግራቸውን ጥለው የጋራ ትርክት በመገንባታቸው ብልጽግናን ተጎናጽፈው በሰላም እየኖሩ ነው ብለዋል፡፡

የጋራ ትርክት ከግላዊ አጨቃጫቂ ችግሮች መውጫ የመፍትሔ መንገድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምም ከኢትዮጵያውያን አልፎ አፍሪካውያንን በሚያኮራ ሁኔታ መገንባቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በትልቅነቱ፣ በጥራቱ እና በውስጡ በያዛቸው ቅርሶች እንደሚገለጽ ነው የተናገሩት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.