ጠመንጃ ታጥቆ የራስን ህዝብ እያሰቃዩ እታገልልሃለሁ ማለት ትርጉም የሌለው አካሄድ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠመንጃ ታጥቆ የራስን ህዝብ እያሰቃዩ እታገልልሃለሁ ማለት ትርጉም የሌለው አካሄድ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰላም እና ፀጥታን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥቄዎች በሰጡት አስተያየት÷ ሰላም ለምናስበው ብልፅግና በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰላም፣ ፀጥታ እና ደህንነት የሚያውኩ ጉዳዮች የፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ ልምምድ ችግር (ፍላጎትን በጠመንጃ ማሳካት መፈለግ)፣ ችግርን የመፍቻ መንገድ፣ የሰላም ጅማሮ ሲኖር በሰላም መንገድ ወጥመድ ማስቀመጥ ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።
እነዚህ ጉዳዮች በኢትዮጵያ አንድነት፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጉዳይ ላይ ተመስርቶ የሚነሳ እና ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጎ የሚነሳ ጉዳይ አይደልም፤ ለግለሰቦች ወይም ለቡድኖች ለግል ጥቅም የሚነሳ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የሰላም ድርድሩ ምን አመጣ፣ ከሰላም ድርድር በኋላ ምን ተገኘ የሚለውን እንጂ ከጦርነቱ ምን አተረፍን የሚለው ብንገመግም መልካም ነበር ብለዋል፡፡
ይህም አበክረን የምንፈልገው ብጥብጥ እንጂ ሰላም አለመሆኑን ማመላከቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሽብርተኛው ሸነኔን በተመለከተም ከለውጡ በፊትም ይሁን በኋላ ለሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች የቀረበው የሰላም ጥሪ አንድ ነው በማለት አንስተዋል።
ከለውጡ በፊትም ይሁን በኋላ ለሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች የቀረበው የሰላም ጥሪ አንድ ነው፤ ኦነግን ወክለው በሃላፊነት ደረጃ አስመራ ንግግር ያደረጉ ሰዎች አብዛኞቹ አዲስ አበባ ነው ያሉት ከፊሎቹም በዚህ መንግስት ውስጥ ተካተው ሃላፊነት ወስደው እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
የተለየ ምክክር እና ድርድር ካለ ግማሾቹ እዚህ ገብተው ስልጣን የሚጋሩበት ከፊሎቹ ደግሞ ጫካ ገብተው ሰው የሚያሰቃዩበት ምንም ምክንያት አይኖርም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ታንዛኒያ የነበረው ድርድር የግልፀኝነት ችግር አለው ብለው የሚያነሱ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ወደ ታንዛኒያ ሄደን ድርድር ስንጀምር ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ድርድር እንደምንጀምር ተገልጿል ብለዋል፡፡
ድርድርድ ከጀመርንም በኋላ ይህንን አሳካን ብለን ለመናገር የሚያስችል ድምዳሜ ላይ ባለመደረሱ ምንም ነገር ማቅረብ አልቻልንም ነው ያሉት፡፡
ወደፊት ግን ልቦና ሰጥቷቸው የኢትዮጵያን ህግ አክብረው በውይይት አምነው ድርድሩ ሲፈፀም በግልፅ ሪፖርት እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ሸኔ በአስመራ የተደረገው ድርድር በመንግስት ሳይሟላ ቀርቶ፤ የተገባው ሳይፈፀም ቀርቶ እና እታገልለታለው ለሚለው ህዝብ ልማት ተጨንቆ ከሆነ ወደ በረሃ የገባው ያንኑ ህዝብ እያገቱ ልማት እንዳይሰራ እያደረጉ ዘረፋ መፈፀም ለኦሮሞ ህዝብ ምንም ፋይዳ የለውም በማለት አስገንዝበዋል።
አሁን ተሰማርቶ ያለበት መኪና እያቃጠሉ እና እያገቱ ዘረፋ መፈፀም በየትኛውም መስፈርት የትግል ማሳኪያ ስልት ተደርጎ አይወሰድም፤ ጥፋት ነውም ብለዋል።
የራስን ህዝብ እያሰቃዩ እታገልልሃለው ማለት አግባብ አይደለም፤ ልቦና ገዝቶ ወደ ሰላም መድረክ እራስን ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ አመልክተዋል።
በጠመንጃ እና በአፈ ሙዝ ከእንግዲህ በኋላ ስልጣን ይዞ ማስተዳደር አይቻልም ሲሉም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡