ቱሪዝም እንጀራ ነው፤ የሥራ ዕድል ፈጣሪም ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቱሪዝም ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ኢንዱስትሪ መሆኑን ስለምናውቅ የመዳረሻ ልማት ሥራዎችን በልዩ ትኩረት እያከናወንን ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቱሪዝምን በተመለከተው ማብራሪያቸውም÷ ቱሪዝምን በሚመለከት የመዳረሻ ልማት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ቱሪዝምን ከገቢ አንጻር ብቻ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው÷ ቱሪዝም የምንመኘውን የኑሮ ዘይቤ ለመውረስ የሚደረግ ጥረት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም መንግስት የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ-መንግስትን በማደስ አንድነት ፓርክን ገንብቶ በአሁኑ ወቅት በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ብር ገቢ አስገብቷል ብለዋል፡፡
ቱሪዝም እንጀራ እና ሥራ ፈጠሪ ነው፤ በዚህ አግባብ መረዳት ይገባል እንጂ በዘርፉ እየተከናወኑ ላሉ የጽዳትና ውበት እንዲሁም የፓርክና መዳረሻ ልማት ሥራዎች ዝቅ ያለ ግምት መሥጠት ተገቢ እንዳልሆነ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ያለውን ምቹ መልከዓ ምድር ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ግዙፍ እና ጥራት ያለውን ለትውልድ የሚሸጋገር የቱሪዝም መዳረሻ ጎርጎራን ገንብተናል ነው ያሉት፡፡
የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትንም ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመነጋገር ጉዳት ሳይደርስበት ለትውለድ የሚያሸጋግር ጥገና እየተሠራ መሆኑን አመላክተው፤ ይህ ሁሉ ሥራ የሚከናወነው መንግሥት የኢትዮጵያን ዕምቅ ሀብትና የቱሪዝሙን ዘርፍ ገቢና ሥራ ፈጣሪነት ስለሚገነዘብ ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሠላም እና ጸጥታ ላይ ካልተሠራ ግን የመዳረሻ ልማት ሥራ ብቻ ለቱሪዝሙ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ላይሰጥ ይችላል፤ ይህንንም ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው