Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ ውጪ ለሶማሊያ ሰላም ሲል የሞተ የለም – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ውጪ ለሶማሊያ ሰላም ሲል በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን መስዋዕት ያደረገ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸ የጎረቤት ሀገራትን አስመልክተው እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በፖሊሲዎቿ ቅድሚያ የምትሰጠው ለጎረቤቶቿ ነው፡፡

እንደአብነት ከሶማሊያ ውጪ በርካታ ሶማሊዎች በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ገልጸው፥ ባህል፣ እምነት እና ሌሎች ብዙ ነገሮች እንጋራለን ብለዋል፡፡

ሶማሊያን የሚያጠፋና የሚያፈራርስ ወይም የሚጎዳ ሃሳብ ኢትዮጵያ ፍጹም እንደሌላትና እንደማይኖራት አረጋግጠዋል።

በዚህም የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የሶማሊያ ሰላም የእኛ ሰላም ነው፤ ወንድም ህዝብ ነው፤ ልማቷ ልማታችን ነው ብለን ስላሰብን ነው ብለዋል፡፡

አክለውም፥ ከኢትዮጵያ ውጪ ለሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን መስዋዕት ያደረገ የለም በማለት አንስተዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊትም ኢትዮጵያ ወታደሮችን አሰልጥና ወደሀገሪቱ መላኳንም ነው አያይዘው የገለጹት፡፡

በዚህም ከሶማሊያ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት አንፈልግም፤ ይልቁንስ በጋራ ትብብር ማደግ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.