Fana: At a Speed of Life!

አይኦኤም ኢትዮጵያ ውጤታማ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራት እገዛ እንደሚያደረግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራት እገዛ እንደሚያደርግ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአይኦኤም ካውንስል ሰብሳቢ፣ በጄኔቫ የጀርመን አምባሳደርና የተባበሩት መንግስታት ቋሚ መልክተኛ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጄኔቫ ወኪል ከሆኑት አምባሳደር ካትሪና ስታሽ ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷ ተመላሽ ዜጎች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ ከተመላሽ ዜጎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እያስከተለ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ተቋማቸው በስፋት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ካትሪና በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም እያደረገች ያለውን ጥረት ማድነቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራት ለማድረግና የሴቶችን አቅም ለመገንባት እገዛ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.