Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የአግሪኮላ ሽልማት ተምሳሌታዊ የአመራር ሰጭነት ውጤት ነው – የቻይና ኤምባሲ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ያበረከተላቸው የአግሪኮላ ሽልማት ተምሳሌታዊ የአመራር ሰጭነት ውጤት መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በጣሊያን ሮም የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሽልማትን መሸለማቸው ይታወቃል።

ሽልማቱ የተሰጣቸውም÷ ፈተናዎችን በመቋቋም በምግብ ዋስትና፣ በተመጣጠነ ምግብና በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል ባላቸው ራዕይ፣ ባሳዩት የአመራር ቁርጠኝነት እና ባመጡት ፈጣን ለውጥ መሆኑን ነው የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በግብርና ልማት አስተዋጽዋቸው ከፋኦ የተበረከተላቸው ሽልማት የተምሳሌታዊ አመራር ሰጭነት ውጤት ነውም ብለዋል።

የቻይና መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአግሪኮላ ሽልማት የተሰማውን ደስታ ገልጸው፥ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ግብርናውን ለማሸጋገር ያለው ቁርጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ምንም ጥርጥር የለውም ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ ከምግብ ዋስትና ችግር በመላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በኩራት ከፍ እንደምትልም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያመጣው ስኬት እንደሆነ ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የኢትዮ-ቻይናን ጠንካራ ትብብርን ይበልጥ በማጎልበት የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡

ብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድምፅ መሆኑን ያነሱት ሺን ቺንሚን፥ ኢትዮጵያና ቻይና በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ለሚያደርጉት ትብብርም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.