37ኛው የሕብረቱ ጉባዔ ከ1 ሺህ በሚልቁ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሽፋን ያገኛል
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ1 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላከተ፡፡
37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ስብሰባውን የሚዘግቡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች የመግቢያ ባጅ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ ሚዲያ አካላት የመዳረሻ ቪዛ ለማመቻቸት እና ለሙያ መሳሪያዎቻቸው የከስተም ክሊራንስ ስራዎችን ለማከናወን እንዲቻልም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ፣ በአፍሪካ ሕብረት ባጅ ሴንተር እንዲሁም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት 24 ሰዓት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ባለሥልጣኑ የአፍሪካ ሕብረት የብሔራዊ የጉባዔ አመቻች ኮሚቴ አባል ሆኖ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን÷ ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ እና ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሂደቱም ጉባዔውን የሚዘግቡ ሚዲያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበት፣ የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነትና መልካም ገጽታ ጎልቶ በሚታይበት መልኩ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ስራ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
እስካሁን ባለው የምዝገባ ሂደትም ከ350 በላይ የሀገር ውስጥ እና 550 የውጭ ጋዜጠኞች ምዝገባ ተካሂዷል መባሉን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀሪ ጊዜያትም ተመዝጋቢ የሚዲያ አካላት ቁጥር እንደሚጨምር ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረጉንም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው፡፡