Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ ሆቴሎች የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት አጠናቅቀዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አስታውቋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን እንዳሉት÷ የመዲናዋ ሆቴሎች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አጠናቅቀዋል፡፡

ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የኢትዮጵያን ባህል እና እሴቶች የሚያንጸባርቁ ሁነቶችን ለእንግዶች እንደሚያሳዩ አንስተዋል፡፡

በተለይም የቡና አፈላል ሥርዓት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ባህላዊ ጭፈራዎች እና ሌሎች ኩነቶችን ለእንግዶች ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሆቴሎች እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንከን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከፖሊስ ጀምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡

ሕብረተሰቡም ለጉባዔው የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የኢትዮጵያ እንግዳ አቀባበል ሥርዓት አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.