ዜጎች የቤት አቅርቦት እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት ባለቤትነት፣ በፌዴራል ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አማካሪነት እና በኦቪድ ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት በባሕር ዳር ከተማ የተገነቡት የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች ተመርቀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተው ሕንጻዎቹን መርቀዋል።
አቶ አረጋ ከበደ÷ ዛሬ የተመረቀው ሕንጻ ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት ቤቶችንም የያዘ በመሆኑ በውስጡ ለሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለከተማው ነዋሪዎችም የላቀ ጥቅም ያለው ነው ብለዋል።
ሕንፃው ከዚህ በፊት ይታይ የነበረውን የግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተት የቀረፈ እና በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ልምድ የተቀሰመበት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ “ዜጎች የቤት አቅርቦት እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” መሆኑን ጠቁመው በባሕር ዳር ተገንብቶ የተመረቀው ዘመናዊ ሕንጻ በሌሎች የክልሉ ከተሞችም ተደራሽ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አበረ ሙጨ በበኩላቸው÷ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባለ ብዙ ወለል ሕንፃዎችን በመገንባት የክልሉን ሕዝብ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተመረቁ ባለ 12 እና ባለ 13 ወለል አራት ሕንፃዎች በትንሽ ቦታ በርካታ መኖሪያ ቤት የመገንባትን ልምድ ያስገኘ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ሕንፃዎቹ በጥራት እና ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በ6 ወራት ተገንብተው የተጠናቁ ሲሆን÷በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ እና 200 ለመኖሪያ እና 36 የንግድ ቤቶችን የያዙ ናቸው ተብሏል።