Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ማን ናቸው?

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህክምና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን÷ በህብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

የስነ ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ዕቅድን ሰብ-ስፔሻላይዝ ያደረጉት ዶ/ር መቅደስ፤ በተማሩበት ሙያ ሰፊ አገልግሎት ሰጥዋል።

ከዚያም ባሻገር በርከት ባሉ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች አጫጭር ኮርሶችና ምስክር ወረቀቶችን በማግኘት ሙያቸውን አዳብረዋል።

በስራ ልምዳቸውም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው በማስተማር አገልግለዋል። እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርት ሃላፊ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የዓለም አቀፍ ስነ-ተዋልዶ ጤና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት ስዊዘርላንድ ጄኔቭ በሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ልዩ ረዳት ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ ነበር።

ዶክተር መቅደስ ዳባ በማኅጸንና ጽንስ ሕክምና ባደረጉት ምርምርና አስተዋጽዖ በፈረንጆቹ 2021 በሴቶች ዘርፍ የዓለም የጽንስና ማኅፀን ሕክምና ሽልማትን ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.