የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ትምህርት ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የካናዳ መንግስት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ትምህርት ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሺኣ ታባህ(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
አምባሳደሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትብብር ስምምነት የሚከናወኑ ተግባራትን ጎብኝተዋል።
አምባሳደሩ እንደገለጹት ፥ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ከካናዳው ኪዩንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለ10 ዓመታት የሚተገበር የ25 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ነው።
የፕሮጀክቱ አፈፃፀምን በተመለከተ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አምባሳደሩ የተወያዩ ሲሆን ÷ የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የካናዳ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ቢንያም ጫቅሉ(ዶ/ር) ÷ ዩኒቨርሲቲው ከካናዳ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም በትምህርት ዘርፉ የሚሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአካል ጉዳተኞች አካቶ ትምህርት የ10 ዓመት ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆኑን የገለፁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ፥ በትምህርት ዘርፍ ሁለቱ ተቋማት የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉም ብለዋል።
የካናዳ ዩኒቨርሲቲዎች ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመሯቸው የትብብር ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በሹመት አለማየሁ