የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ለትግራይ ክልል የ67 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በትግራይ ክልል በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሚውል የ67 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የተመራ ልዑክ በመቀሌ ከተማ በመገኘት ድጋፍ አበርክቷል፡፡
በዚህም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል የ67 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ድጋፉ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና ግለሰቦች የተገኘ ሲሆን÷ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ምግብ ነክ እና መድሐኒት እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ÷ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የተደረገው ድጋፍም ወንድማዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር እንደሆነ መግለጻቸውን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡