የገዥው ፓርቲ አባል ሳይሆኑ እንዲያገለግሉ እድል መስጠት የሀገርን ጥቅም ያስቀደመ ውሳኔ ነው – የምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገዥው ፓርቲ አባል ሳይሆኑ በመሾም እንዲያገለግሉ እድል መስጠት ከምንም በላይ የሀገርን ጥቅም ያስቀደመ ውሳኔ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባለት ገለጹ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ከተሿሚዎቹ መካከል አምባሳደር ታዬ እና ዶክተር መቅደስ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ አባል ሳይሆኑ የተሾሙ ናቸው።
ይህን ተከትሎ የምክር ቤት አባላት የሆኑት ፈቲህ መዕዲ (ዶ/ር)፣ አቶ መለሰ መና እና ነጃት ግርማ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት÷ የፓርቲው አባል ሳይሆኑ በእውቀትና ልምዳቸው እንዲያገለግሉ መደረጉ ከስልጣን ይልቅ ሀገርን ያስቀደመ ድንቅ ውሳኔ ነው ብለዋል።
የገዥው ብልጽግና ፓርቲ አባል ያልሆኑና የየትኛውም ፓርቲ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች በእውቀትና ክህሎታቸው እየተመረጡ መሾማቸው ሀገርን ከማገልገል ባለፈ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሀገር ልማትና ዕድገት ላይ አሻራቸውን ያሳርፋሉ የተባሉ ግለሰቦች መሾማቸው ከምንም በላይ ሀገርን ያስቀደመ ውሳኔ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግርን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሚደረገው ሂደት እንዲህ አይነት ሹመቶች ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።
በቀጣይም ሀገርና ህዝብን በእውቀታቸውና በልምዳቸው ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰዎችን ወደ ፊት ማምጣት ይገባል ብለዋል።