Fana: At a Speed of Life!

እውቁ ኢትዮጵያዊ የናሳ ተመራማሪ ‘ፍቅር’ የሚል የፈጠራ ስራ አስተዋወቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዋቂው የናሳ ተመራማሪ ብርሀኑ ቡልቻ (ዶ/ር) ‘ፍቅር’ የሚል ኢትዮጵያዊ ስያሜ የሰጡትን የፈጠራ ስራ አስተዋወቁ፡፡

ብርሀኑ ቡልቻ(ዶ/ር) ከህዋ ቴክኖሎጂ ምርምራቸው ጋር በተያያዘ በርቀት ካሉ የህዋ አካላት የሚወጡ የኢንፍራሬድ ቅንጣት ምስሎችን መዝግቦ የሚያስቀርና ‘ፍቅር’ የሚል አዲስ የፈጠራ ስራ ማስተዋወቃቸው ተሰምቷል፡፡

ተመራማሪው ‘ዘ ኢኖቬሽን ካታሊስት’ በሚል ርዕስ ከሚታተመው የናሳ መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም ÷ ‘ፍቅር’ የተሰኘው የፈጠራ ስራ ባለንበት ሶላር ሲስተምና ከዛም ባሻገር ያሉ ጨረቃዎች የሚያመነጯቸውን የብርሀን ቅንጣቶች ዓይነትና ይዘት በመለየት በህዋ አካላቱ ውስጥ ህይወትን መደገፍ የሚያስችል ነገር መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ያገለግላል ብለዋል።

ተመራማሪው ስለ አዲሱ ግኝታቸው ኢትዮጵያዊ ስያሜ ‘‘ለሀገሬ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ ነው’’ ማለታቸውን ከዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በስራው እገዛ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና ያቀረቡት ተመራማሪው ÷ ስራቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ለተሻለ ፈጠራ የሚያነሳሳ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

ብርሀኑ ቡልቻ( ዶ/ር) ከዚህ በፊት በጨረቃ ላይ ውሀ መኖሩን የሚያጣራ መሳሪያ መፍጠራቸው ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.