“ፖለቲካችን ከነፍጥ ትግል ወደ ሃሳብ ትግል መቀየር አለበት” – አቶ ሳዳት ነሻ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)”ፖለቲካችን ከነፍጥ ትግል ወደ ሃሳብ ትግል መቀየር አለበት”ሲሉ የብልፅግና ሥራ አስፈፃሚ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ገለጹ፡፡
“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የደምቢ ዶሎ ከተማና የቄለም ወለጋ ዞን ነዋሪዎችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
አቶ ሳዳት ነሻ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷”ፖለቲካችን ከነፍጥ ትግል ወደ ሃሳብ ትግል መቀየር አለበት” ፤ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ መንግስት በብዙ ዋጋ ተጨባጭ ሥራዎችን ሰርቷል።
ለሽብር ቡድኑ ሸኔ በተደጋጋሚ የቀረበው የሰላም በር አሁንም ክፍት መሆኑን ነው በአጽንኦት የተናገሩት ፡፡
ነገር ግን ይህን ዕድል አሻፈረኝ በማለት የኦሮሞን ሕዝብ ዳግም ወደ ጨለማ ለመመለስ፣ ለመዝረፍ፣ ለመግደልና ለማፈናቀል የሚጥር አካልን መንግስት የማይታገስና ህግና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነቱን የሚወጣ ይሆናል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኤሌማ አቡበከር በበኩላቸው ÷የብልፅግና ፓርቲ በተለያዩ ዘረፎች የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን እየመለሰ ይገኛል ብለዋል።
የኦሮሚያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ያለውን ቁርጠኝነት የተረዳ ፅንፈኛ ቡድን በዚህ ህዝብ መካከል ሰላምና አንድነት እንዳይኖር ለዓመታት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የዞኑ ህዝብ ከአመራሩና ከፀጥታ ጋር በከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ያገኘውን አንፃራዊ ሰላምና የልማት ዕድሎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜ በበኩላቸው÷ መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን ያለ ዘላቂ ሰላም ግን የተጀመሩትን ማጠናቀቅ ፤ አዲስ የሚነሱትን ጥያቄዎች መመለስ አይቻልም ብለዋል።
በዚህም የታየውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠልና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ህዝቡ ፅንፈኝነትንና የትጥቅ ትግል አራማጆች ላይ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።
የሸኔ ሽብር ቡድን የጭካኔና የጥፋት ተግባራት ከቄለም ወለጋ ዞን ሕብረተሰብ በላይ ገፈት ቀማሽና ምስክር የለም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በመራኦል ከድር
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_televisionበመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!