ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ 28 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደጎም የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ 28 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት እቅድ አፈፃጸሙን ከዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻዎች ጋር “ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል ተወዳዳሪነትን እናስፍን” በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየገመገመ ነው፡፡
የሚኒስቴሩን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ ኡርጌሳ ባይሳ የድጎማ ስርዓቱ ተግባራዊ መደረግ መንግስት የነበረበትን 180 ቢሊየን ብር በማቃለል ወደ 117 ነጥብ5 ቢሊየን ብር ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የድጎማ ስርዓቱ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ 199 ሺህ 333 ተሸከርካሪዎች የስርዓቱ ተጠቃሚ መሆናቸውም ነው የተጠቆመው፡፡
በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሚሊየን 19 ሺህ 455 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል ተብሏል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በዚህ ወቅት፥ ወጥነት ያለው የተናበበና የተቀናጀ አሰራር በመዘርጋት የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የንግድ አሰራርን በማዘመን ተደራሽና ፍትሐዊ ውድደር የሰፈነበት በማድረግ፣ ለገበያ የሚቀርቡ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን የጥራት ደረጃ በማዘጋጀትና ተግባራዊነቱን በመቆጣጠር የሸማቹን ብሎም የንግዱን ማህበረሰብና የሀገርን ጥቅምና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የንግድ ስርዓት መገንባት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
አክለውም፥ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሽፋን ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረበት 57 በመቶ ባለፉት 6 ወራት ወደ 89 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ነው ያስረዱት ሚኒስትሩ፡፡
ይህም የንግድ ማህበረሰቡ የነበረበትን እንግልት፣ ወጪ እና የጊዜ ብክነት በማስቀረት የደንበኛ እርካታን ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡
በሌላ መልኩ የድህረ ፈቃድ ክትትልና ቁጥጥር ስራው የተሟላ ባለመሆኑና የሚወሰደው እርምጃ የተጠናከረ ባለመሆኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚነግዱ፣ ፈቃድ ሳያሳድሱ እንዲሁም ከዘርፍ ውጪ የሚነግዱ በመኖራቸው በቀጣይ ክትትልና ቁጥጥሩን በማጠናከር አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሚሊየን 381 ሺህ 938 አገልግሎቶች በኦንላይ የተሰጡ ሲሆን፥ ይህ አፈፃጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ69 በመቶ ብልጫ እንዳለው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡