የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር መንግስት ጥረት እያደረገ ነው – አምባሳደር ምስጋኑ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ በጀርመን ፓርላማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የእርስ በርስ ግጭት መከላከል ኮሚቴ ሃላፊ ከሆኑት ሞኒካ ግራተርስ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ኢትዮጵያና ጀርመን ረጅም ጊዜያትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አምባሳደር ምስጋኑ አንስተዋል፡፡
ሀገራቱ በኢኮኖሚያ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በሀገራዊ ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመቋጨት የተደረሰው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመተባባር በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
ሚስ ሞኒካ ግራተርስ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ እና የጀርመንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ትብብር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡