Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።

ስብሰባው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“ በሚል ሕብረቱ ባዘጋጀው የ2024 መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።

በስብሰባው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የኅብረቱ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።

ምክር ቤቱ በዋናነት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ለማፋጠን ባለፈው አንድ ዓመት የተሰራውን ሥራ በተመለከተ በሚቀርበው ሪፖርት ላይ ምክክር ያካሄዳል።

በተለይም ነጻ የንግድ ቀጣናውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የኃብት ማሰባሰብ ሥራዎች፣ ቅንጅታዊ አሰራር፣ በታሪፍና የንግድ ሰንሰለት ዙሪያ በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያም እንደሚመክር ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የህብረት ከሀገራትና ከባለብዙ ወገን ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነት በተመለከተ በሚደነግገው ረቂቅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ እንደሚወያይም ይጠበቃል።

የአፍሪካ የሰላም ፈንድ ወደ ሥራ ለማስገባት በኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር የሚቀርበው ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ተጠቁሟል።

አባል ሀገራቱ ለሠላም ፈንዱ በመዋጮ 400 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰበ ቢያቅዱም አሁን ላይ ፈንዱ 361 ሚሊየን ዶላር ገደማ ነው ሊሰበሰብ የቻለው።

ምክር ቤቱ ከጥር 6 እስከ 17 ቀን 2016 ዓ.ም የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይም ይወያያል።

በአፍሪካ ኅብረትና በተቋማቱ የተከናወኑ ሥራዎች፣ በተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም አፍሪካ ኅብረት በቡድን 20 እንዴት መሳተፍ አለባት በሚሉ ጉዳዮች ላይም ምክክር እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡

የአስፈጻሚ ምክር ቤቱ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.