በግብርናው ዘርፍ አሁንም ብዙ የቤት ሥራ አለብን – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው ዘርፍ የተሰራው ሥራ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም ብዙ የቤት ሥራ አለብን ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ባቀረቡት ሪፖርት ነው፡፡
በሪፖርታቸውም በግብርናው ዘርፍ በ2015/16 የበልግ እርሻ ከ61 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልፀዋል።
በመኸር እርሻ 91 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ያቀደው ክልሉ 95 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የቻለ ሲሆን ፥ እስካሁን ከ942 ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በመስኖ ልማት 48 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በመጀመሪያ ዙር መልማቱን የገለጹት አቶ ደስታ ፥ በበጋ ስንዴ ልማት 130 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል።
ክልሉ በቡና ምርት ተወዳዳሪ እንዲሆን በተደረገው እንቅስቃሴ የምርጥ ዘር አቅርቦትና ለአርሶ አደሩ በተሰጠው ስልጠና ከአንድ ሄክታር 9 ነጥብ 4 ኩንታል ቡና ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
ክልሉም በዘንድሮ ዓመት 125 ሺህ ቶን ቡና መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 6 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል ተብሏል።
በእንስሳት ሃብት ልማትም የተሻለ አፈፃፀም አሳይተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ በዘንድሮ ዓመት ከ102 ሺህ በላይ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።
ክልሉ 76 ነጥብ 8 ቶን የተፈጥሮ አፈር ማደበሪያ (ኮምፖስት) በማዘጋጀት ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉንም አንስተዋል፡፡
በጥላሁን ይላማ እና ታመነ አረጋ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!