Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጻም ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች የአፈጻጻም ግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያ የኢኒሼቲቩ ትልቋ ተጠቃሚና የቀጣናውም የሰላምና የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኗን የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበርና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ አስረድተዋል፡፡

በመድረኩም በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ÷ በግብርና፣ ጤና፣ መንገድ፣ ውሀና ኃይል አቅርቦት፣ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ እንዲሁም በዲጂታል ኮሙኒኬሽን የሚከናወኑ 14 ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች ቀርበው ተገምግመዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም የአፈጻጸም አቅጣጫም መቀመጡን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት÷ ኤርትራን፣ ጅቡቲን፣ ኬንያን፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን በማቀፍ ከአራት ዓመታት በፊት የተመሰረተ ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የኢኒሼቲቩ አስተባባሪና መሥራች መሆኗን አስታውሰው÷ በምሥራቅ አፍሪካ በኢኮኖሚም ሆነ በሁለንተናዊ መልኩ ግንባር ቀደም በመሆን ለቀጣናው ሀገራት አርአያ ናት ብለዋል፡፡

በኢኒሼቲቩ የገንዘብ ድጋፍ በሀገሪቱ የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የግብርና፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን የመቋቋም ቀጣናዊ ፕሮጀክቶችን ከተያዘላቸው ጊዜ በግማሽ በማሳጠርና የተመደበውን በጀት በቁጠባና በጥንቃቄ በመጠቀም ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡

የምክክር መድረኩም በቋሚነት በየሦስት ወሩ እንዲካሄድና የቀጣናዊ ፕሮጀክት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን በየወሩ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.