በዲላ፣ ወላይታ ሶዶና አርባምንጭ ከተሞች ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ፣ ወላይታ ሶዶና አርባንጭ ከተሞች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
መድረኩ “ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካደው፡፡
በዲላ ከተማ በተካሄደው መድረክ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳዳር ተስፋዬ ይገዙ እንዲሁም በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ውሀ ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) እየመሩት ይገኛሉ።
አቶ ይርጋ በመድረኩ እንዳሉት፥ የህዝቦች ወንድማማችነት እና አብሮነት በጋራ ጥረት ወደ ፊት ይራመዳል ብለዋል።
የልማት ተግባሮቻችንን አንድ ከሆንንና ከተባበርን የምንፈልግበት ደረጃ ማድረስ እንችላለን ሲሉም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም በፈታኝ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ር/ መስተዳደር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፥ ችግሩን ተቋቁመን ለመሻገር የዜጎች ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማም ህብረተሰቡ ያሉበትን ጥያቄዎች ለሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች በቀጥታ ማቅረብ እንዲችል ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር)፥ በዞኑ ያሉ ሃብቶችን በመጠቀም የዜጎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ ወላይታ ሶዶ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረኩ የተካሄደ ሲሆን፥ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ተገኝተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በውይይት መድረኩ ተገኝተዋል።
መድረኩ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞን ለማጠናከር እና ተግዳሮቶችን በውይይትና በትብብር ለመፍታት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑም ታምኖበታል።
በተጨማሪም ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትን ፅኑ መሰረት ላይ ለመትከል መድረኩ ሚናው የጎላ መሆኑም ተጠቁሟል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ፣ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች እና የከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
እንዲሁም በክልሉ አርባምንጭ ከተማ ተመሳሳይ ህዝባዊ የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን ፥ በመድረኩ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፣ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የአርባምንጭ ከተማ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደረጀ ጳውሎስ ለመድረኩ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳብ በቤቶች ልማት፣ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት፣ የሥራ አጥነት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአሸብር ካሳሁን እና አበበች ኬሻሞ