Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – አቶ አሕመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርት እንቅስቃሴን ለማስፋት እና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር ) እና የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻየ ሐዋሳ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ አሕመድ ሺዴ በማብራሪያቸው÷ ከልማት ጋር በተያያዘ እየተተገበሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ወደ ታች እንዲወርዱ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በቀጣይ በሚሰሩ ተግባራት እውን ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በመንገድ ልማት ላይ መንግስት እየሰራበት እንደሚገኝ በመጥቀስ የሰላም ችግር የሚታይባቸው ክልሎች ላይ በበለጠ ሰላም ላይ መስራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ችግሩ እንዲፈታ መንግስት ለሰላም ድርድር ሁሌም ዝግጁ ነው ያሉት አቶ አሕመድ ሺዴ÷ ከኢኮኖሚ አንፃርም የምርት እንቅስቃሴን ማስፋት እና ያሉ የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የመቀላቀሏ ጉዳይ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ በንግድ፣ በፋይናንስ አቅርቦትና በመሰል ጉዳዮች ላይ ትልቅ አበርክቶ ያለው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው÷ ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳደግ በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ አንስተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ወጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር ) በበኩላቸው÷ በህዝቡ ከተነሱት ሀሳቦች ውስጥ የክልሉ ሰላም መጠበቁ የጋራ ጥረት ውጤት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

የውይይት ተሳታፊዎች ባነሱት ሀሳብም÷ አመራሩ ወርዶ ከህዝቡ ጋር ለመነጋገር እያደረገ ያለውን አካሄድ አድንቀዋል፡፡

በልማት ስራ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ወደ ታች ማውረድ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ የኢኮኖሚ ተግዳሮት ህዝቡን እየፈተነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የመንገድ ችግር ያሉባቸው አካባቢዎች መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፤ በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የታጠቁ ሀይሎችም ለሰላም ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.