Fana: At a Speed of Life!

የቀደመው ስርዓት ያሻገረውን ዕዳ ወደ ምንዳ መቀየር ይገባል – አቶ አለማየሁ ባውዲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀደመው የፖለቲካ ስርዓታችን አሻግሮ የሰጠንን ዕዳ በውይይት ላይ በተመሠረተ ጥረት ወደ ምንዳ ልንቀይረው ይገባል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ተናገሩ።
 
“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በጋሞ ዞን ሠላም በር ከተማ ተካሄዷል።
 
በመድረኩ ላይ አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ ኢትዮጵያ ጠላቷ የሆኑትን የፖለቲካ፣ የልማትና የማሕበራዊ አኗኗር ስብራት በመጠገን ለመበልፀግ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
 
ለዚህ ደግሞ ሠላም ዋናው ጉዳይ በመሆኑ የጋሞ አባቶች ለዘመናት ያቆዩት የዱቡሻ ባህል መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
 
በዚህም ባለፈው ምርጫ በብልፅግና ፓርቲና በቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በጋሞ አባቶችና በተለያዩ አካላት ጥረት በውይይት ተፈትቶ መግባባት ላይ መደረሱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የቀደመው የፖለቲካ ስርዓታችን አሻግሮ የሰጠንን ዕዳ በውይይት ወደ ምንዳ ልንቀይረው ይገባል ሲሉም ነው ኃላፊው የገለፁት።
 
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት አሰፋ በበኩላቸው የፓርቲዎቹ ችግር በምክክር እልባት ማግኘቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዩነትን አቻችለው እንዲፎካከሩ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
 
ፓርቲዎቹ ወደ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው በትብብር ለመስራት ቃል መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
 
የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሳዬ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሠላም ዋና መሣሪያ መሆኑን ገልጸው፤ ሠላምን ማስጠበቅ የሁሉም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ብለዋል።
 
በመለሰ ታደለ
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.