Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ  ተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ ከየካቲት 3 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል።

አገልግሎቱ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የምዝገባ ሂደትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ÷የካቲት 3 የተጀመረው ምዝገባ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ አስታውቋል፡፡

ዘንድሮ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ገልጸዋል።

ከዝግጅቱ መካከልም የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን መመዝገብ የሚያስችል ስራ ማከናወን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ምዝገባ የጀመሩ አካባቢዎች መኖራቸውን በመግለጽ በቀጣይም ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች ምዝገባውን እንደሚያካሄዱ ገልፀዋል።

ፈተናው ላይ ለመቀመጥ በመደበኛ፣ በማታ፣ በርቀት እና በግል በሀገር አቀፍ ደረጃ መመዝገብ ከሚያስችሉ መስፈርቶች መካከል ዋነኛው የትምህርት ማስረጃ መሆኑን ተናግረዋል።

በመደበኛ እና በማታ ትምህርት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ በትምህርት ቤቶች እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

የግል፣ የርቀት እና በበይነ መረብ ተምረው የሚፈተኑ ተማሪዎች ምዝገባ በክፍለ ከተማ፣ በልዩ ወረዳ እና በወረዳ የትምህርት ፅ/ቤቶች እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ2016 በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ከ870 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.