የህዝብን ቅሬታዎች ለመፍታት ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ጋር በትብብር እየሰሩ ነው – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብን ቅሬታዎች ለመፍታት ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት እና በትብብር እየሰሩ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡
“ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በመሰረተ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በሰላምና ጸጥታ ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመንገድ፣ የመብራት፣ የኔትወርክ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የትምህርት ቤት፣ የማረሚያ ቤት ግንባታ እንዲስፋፋም ጠይቀዋል።
የገበያ ማዕከሎች፣ የቁም እንስሳት የሕክምና ማዕከል፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ የወተት ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎዎች እንዲቀርቡ እና የቀብሪደሃር ኤርፖርት ወደ ሥራ እንዲገባ አንስተዋል።
ነዋሪዎቹ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች እንዲብራሩም ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ለውጡ ተጠቃሚ ካደረጋቸው ክልሎች ውስጥ ሶማሌ ክልል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በጊዜ ሂደት እየፈታ ይሄዳልም ነው ያሉት።
የህዝብን ቅሬታዎች ለመፍታት ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ ፍስሐ ይታገሱ በበኩላቸው÷በፖለቲካ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በክልሉ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ እየተገነባ መሆኑን በመግለጽ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን እንዲችልም የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከል እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡
የቀብሪደሃር ኤርፖርትን ወደ ሥራ ለማስገባትም ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመነጋገሩ በቅርቡ ዕልባት እንደሚያገኝ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱራህማን አሕመድ አንስተዋል።
በመሳፍንት እያዩ