1 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ግምት ያላቸው ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) ንቅናቄው በፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከድህነት በዘላቂነት መላቀቂያ ቁልፍ መሆኑን በመገንዘብ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በየደረጃው ያለው አመራር አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረጉ በዘርፉ አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑ ተገልጿል።
ለዘርፉ በተደረጉ ድጋፎች በ2015 በጀት ዓመት 544 ሺህ ኪሎ ዋት ኃይል የቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 291 ሺህ ኪሎ ዋት የመብራት ኃይል ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በ2015 በጀት ዓመት 60 ቢሊየን ብር ብድር ቀርቦ የነበረ ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለከፍተኛ አምራቾች ቀርቧል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዶክተር አያና አክለውም፤ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተዘግተው ከነበሩ 446 አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተሰራ ቅንጅታዊ ስራ 390 የሚሆኑትን ወደ ስራ መመለስ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የአምራቾች የማምረት አቅም በመሻሻሉም በስድስት ወራት 994 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ግምት ያላቸው ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጭን ማዳን ተችሏል ብለዋል።