37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባዔው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።
በጉባኤው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።
የመሪዎቹ ጉባኤ የካቲት 6 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም 44ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ በስፋት የሚመክርም ይሆናል።
አህጉራዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ንግድና ትስስር፣ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ ትምህርት፣ ግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ውይይት የሚደረግባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች መሆናቸው ተገልጿል።