ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና አጋር አካላት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አጋር አካላት ለትምህርት ዘርፉ ይበልጥ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የ49 ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች የተሳተፉበት 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ የሀገር እድገትን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትምህርት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ትርጉም ያለው መሻሻል ማሳየቷን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም 30 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ በጀት ፈሰስ በማድረግ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመው ÷ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት እጥረት ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት፡፡
ስለሆነም በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አጋር አካላት ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም እና መረጋጋት ለኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት መሰረቶች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ኢትዮጵያ የቀጣናው እና የዓለም ትብበር ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን እንደምታምን አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ