የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከአልጄሪያ አምባሳደር ሳላህ ፍራንሲስ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ከሆኑት ከሳላህ ፍራንሲስ አልሃምዲን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ ገዱ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳለቸው በመግለጽ ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገሮች ያላቸውን የካበተ የዲፕሎማሲ ልምድ በስልጠናና ልምድ ልውውጥ ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸውም አቶ ገዱ አንስተዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቿን በአርብኛ ቋንቋ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠና በስፋት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቋን በማንሳት አልጄሪያ በዚህ በኩል ድጋፍ እንድታደርግምጠይቀዋል።
ከዚያም ባለፈ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እና ሶስቱ አገሮች እያደረጉት ያለውን ውይይት በተመለከተም አቶ ገዱ ገለጻ አድርገል።
አምባሳደር ሳላህ ፍራንሲስ አልሃምዲን በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በበርካታ ጉዳዮቸ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን በማስታውስ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቿን በአረብኛ ቋንቋ ለማሰልጠን እያደረገች ለላው እንቅሰቀሴ አልጄሪያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን በመጠቀም ልማቷን የማፋጠንና ህዝበቿን ከድህነት የማውጣት ሙሉ መብት እንዳላት አልጀሪያ ትገነዘባለችም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በመርህ ላይ በተመሰረተ ውይይት መፍታት አለባቸው ብላ አልጀሪያ እንደምታምንም አምባሳደር ሳላህ መግለጻቸውን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።