በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና አቅም ለማጎልበት እንሠራለን- የአፍሪካ የሥጋት አሥተዳደር ግሩፕ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና አቅም ለማጎልበት እንደሚሠራ የአፍሪካ የሥጋት አሥተዳደር ግሩፕ አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊና የአፍሪካ የሥጋት አሥተዳደር ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂማ ዲዮንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግብርና ሥርዓት ለመገንባት ከአፍሪካ የሥጋት አሥተዳደር ግሩፕ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ኢብራሂማ ዲዮንግ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ስጋት አሥተዳደር ግሩፕ አባል እንደመሆኗ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከመንግሥት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ያለውን የግብርና አቅም ለማጎልበት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተደራጀና ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው÷ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርኅ መሰረትም ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች የአኅጉሩ ሀገራት ለማከፈል እንደሚሠሩ አመላክተዋል፡፡