የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የሚያገለግሉ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለደቡብ ሱዳን እርዳታ አደረገች

By Meseret Demissu

June 04, 2020

አዲስ አበባ፣ግንቦት 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የሚያገለግሉ 17 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን የሕክምና ቁሳቁሶችን ለደቡብ ሱዳን እርዳታ አድርጋለች።

የልዑካን ቡድኑ መሪ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ  አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን÷ የሕክምና ቁሳቁሶቹን የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ለሆኑት ለአምባሳደር ማየን ዱወት ውዎ አስረክበዋል።

እርዳታውን ይዞ የሄደው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ጁባ ሲደርስ  የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አምባሳደር ቢያትሪስ ካሚሣ ዋኒ ጁባ አለም አቀፍ ኤርፖርት በመገኘት አቀባበል አድርገውለታል።

እርዳታውን የተረከቡት አምባሳደር ማየን ኢትዮጵያ በዚህ ፈታኝ ወቅት ኮቪድ-19ን ለመግታት የሚያገለግሉ የህክም ቁሳቁሶች እርዳታ ማድረጓን አድንቀው÷ እርዳታው የሁለቱ አገራት ወንድማዊ ወዳጅነትን የሚያመላክት ነው ማለታቸውን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።