Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ሀገራት ገንዘብ በማተምና ማዕድናትን በመያዝ ወንጀል የተከሰሱ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ሀገራት ገንዘብ በማተምና የተለያዩ ማዕድናትን በመያዝ ወንጀል የተከሰሱ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

ብይኑን የሰጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ 8ኛ የገቢዎችና ጉምሩክ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

1ኛ ተከሳሽ የፀሐይ ሪል ስቴት መስራች፣ ባለድርሻ እና ሥራ አስኪያጅ ቺያን ኩዊን በቀረቡባቸው ክሶች እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን÷ ሌሎች 8 ተከሳሾች ግን የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር በሚል ክስ ብቻ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ብይን ከተሰጠባቸው ተከሳሾች መካከል÷ ቺያን ኩዊን፣ በፀሐይ ሪል ስቴት ውስጥ በተለያየ የግንባታ ሥራ ላይ ሲሠሩ ነበሩ የተባሉት ቻን ዩቻንግ፣ ሊ ሳዩ፣ ሊ ሻን ሎንግ፣ ዚ ሀይ ሎንግ እና ጂን ባኦ ኩዋን ይገኙበታል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ተሳትፎ ጠቅሶ ተደራራቢ ክሶችን ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

አንደኛው ክስም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ነው፡፡

ይኸውም የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና አንቀጽ 356 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ፀሐይ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር 11ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቤት ውስጥ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በጋራ ሆነው ከነሐሴ 24 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሐሰተኛ ገንዘብ ለማተም የሚያገለግሉ መሣሪያዎች፣ ኬሚካሎች እና ወረቀቶች በመጠቀም ሐሰተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘብ፣ የአሜሪካ ዶላር፣ ዩሮ፣ የእንግሊዝ ፓውንድ፣ የቻይና ዩዋን እና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦችን አመሳስለው በማተም ላይ እያሉ በቁጥጥ ስር ውለዋል በሚል ክሱ ቀርቦባቸው ነበር።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ በእነዚሁ ስድስት ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 32/ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና አንቀጽ 371 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ፣ ተከሳሾቹ በሚኖሩበት እና በሚጠቀሙት መኖሪያ ቤት ውስጥ ገንዘብ ለማተም የሚያገለግሉ 2 የብር ማተሚያ ማሽንና የተለያዩ ኬሚካሎች፣ 60 ሚሊየን 750 ሺህ ብር የሚገመቱ ነጭ ወረቀቶች፣ 424 ሺህ አረንጓዴ ወረቀትን ጨምሮ የተለያዩ ለህትመት የሚያገለግሉ ግብዓቶች በፀጥታ አካላት በተደረገ ክትትል ይዘው መገኘታቸውን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ ሐሰተኛ ነገሮችን ለመሥራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች መያዝ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በሌላ በኩል ሦስተኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሸ ላይ ብቻ የቀረበ ነው፡፡

በዚህም የወንጀል ሕግ አንቀፅ 359 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ፍተሻ ሐሰተኛ የሆኑ 297 ሺህ 400 የአሜሪካ ዶላር ባለ 100 ኖት፣ 36 ሺህ 250 የእንግሊዝ ፓውንድ ባለ 50 ኖት፣ 62 ሺህ ባለ 500 ኖት ዩሮ እንዲሁም 65ዐ ሺህ 600 ዩሮ ባለ 200 ኖት እና 1 ሺህ 567 የቻይና ዩዋን ይዞ የተገኘ መሆኑ ተጠቅሶ፤ ሐሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 26/1/መ በመተላለፍ ተከሳሹ በመኖሪያ ቤቱ እና በቢሮ ነሐሴ 25 እና ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በፀጥታ አካላት በተደረገ ብርበራ 1 ሺህ 245 የአሜሪካ ዶላር እና 200 የዓረብ ኤምሬቶች ድርሃም ይዞ መገኘቱ ተጠቅሶ፥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የውጭ ሀገር ገንዘብ መመንዘርና የማዘዋወር ፈቃድ ሳይሰጠው የውጭ ሀገር ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ መያዝ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ በሌላ 5ኛ ክስ ላይ ማዕድን የመያዝ ፈቃድ ሳይኖረው ክብደቱ 108 ነጥብ 43 ኪሎ ግራም እና 51 ነጥብ 88 ኪሎ ግራም ኦፓል የተፈጥሮ ማዕድናትን፣ 4 ነጥብ 99 ኪሎ ግራም ኳርትዝ ማዕድን፣ 77 ነጥብ 71 ኪሎ ግራም አጌት የተፈጥሮ ማዕድን እና 104 ነጥብ 59 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማግኔታይት የተፈጥሮ ማዕድን ይዞ መገኘቱ በክስ ዝርዝሩ የተጠቀሰ ሲሆን÷ ፈቃድ ሳይኖረው የተፈጥሮ ማዕድን መያዝ እና የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፍ ወንጀል ተከሶ ነበር።

በተጨማሪም ይኸው 1ኛ ተከሳሽ በኮንትሮባንድ ወንጀል ክስም ቀርቦበታል።

እንዲሁም 6ኛ ክስ ላይ ከ2ኛ እስከ 9ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፥ በክሱ ላይ እንደተመላከተው የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሀገር ውስጥ ሲኖሩ የተያዙ በመሆኑ በፈፀሙት የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ተደራራቢ የወንጀል ክሶችን በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ በዐቃቤ ሕግ በኩል የዋስትና ጥያቄያቸው ላይ የመቃወሚያ መከራከሪያ ነጥቦች አንስቶ ክርክር ተደርጎል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ ክርክሩን መርምሮ የተከሳሾቹን የዋስትና መብት በመገደብ ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል።

ከዚህ በኋላ ተከሳሾቹ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የሠነድና የሰው ምስክሮችን ቃል በተለያዩ ቀናት አዳምጧል ።

ይህን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ የፀሐይ ሪል ስቴት መስራች፣ ባለድርሻ እና ሥራ አስኪያጅ ቺያን ኩዊን በቀረቡባቸው ሁሉም ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ከ2ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ቀርቦባቸው የነበረውን 1ኛ እና 2ኛ ክስን በሚመለከት “የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው ማስረጃ በበቂ አልቀረበም” በማለት ሁለት ክስ ነጻ ብሏቸዋል።

የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር የወንጀል ክስ ብቻ እንዲከላከሉም ብይን ተሰጥቷል።

ሌሎች ከ7ኛ እስከ 9ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ሦስት ተከሳሾችን በሚመለከትም የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር በሚል በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

እንዲሁም ከ2ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ጠበቆች ዛሬ ይከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ መሰረት የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጥያቄ አቅርበዋል።

ይከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ ዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠትና የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝርን ለመጠባበቅም ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.