Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ አመት፣ 5ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የክልል መስተዳድር ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻፀም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ቀርቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በበጀት ዓመቱ 106 የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በግማሽ ዓመቱ 2 ቢሊየን 131 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ318 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ ከ168 ሺህ ኩንታል በላይ የማሽላና የበቆሎ ምርት መገኘቱንም ገልጸው፤ በመኸር 475 ሄክታር መሬት በስንዴ እንዲሸፈን በማድረግ ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ለማሳካት በተሰራው ስራ ስምንት የዶሮ መንደሮች ማደራጀት መቻሉንና 2 ሺህ 640 የወተት ላሞች እንዲዳቀሉ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 5 ሺህ 547 ስራ ፈላጊዎችን መመዝገብ መቻሉን፣ ለ3 ሺህ 895 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ስለመፈጠሩና ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ስለመሰራጨቱም በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም በተዘዋዋሪ ብድር ተሰራጭቶ የነበረን 38 ሚሊየን ብር ማስመለስ መቻሉን አቶ ኦርዲን በድሪ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.