ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በአሰላ ከተማ ለሚገነባው አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በባለሃብት ተሳትፎ ለሚገነባው የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማትን መገንባት ብቁ የሆነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ትምህርትን ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተው÷ ይህ ትምህርት ቤት በግለሰብ ደረጃ የሚገነባ የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት ነው ብለዋል።
መሰል ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርትን ለመስጠት አስተዋጽአቸው የጎላ እንደሆነ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትምህርት ሚኒስቴርና ክልሉ ላደረገው ጥሪ ባለሃብቱ አቶ ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ ለሠጡት ምላሽ አመስግነዋል።
የትምህርት ሥራ በመንግስት ብቻ የሚሠራ እንዳልሆነ ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በአቶ ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ የሚገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአቅመ ደካማ ወላጅ አልባ ህፃናት አገልግሎት የሚሠጥ መሆኑም ተጠቁሟል።