የሀገር ውስጥ ዜና

የአንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ሥርዓተ-ቀብር ተፈጸመ

By Feven Bishaw

February 23, 2024

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ የሚታወቀው አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡

ድምፃዊው ባደረበት ህመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ኅብረት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ያዘጋጁት የስንብት ሥነ-ሥርዓት÷ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የሙያ አጋሮቹ፣ ዘመድ ወዳጆቹ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

ከስንብቱ በኋላም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የቆየው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር፡፡

ድምጻዊው ለአድማጭ ካበረከታቸው በርካታ ሥራዎቹ መካከል÷ ኢትዮጵያን አትንኳት፣ አዲስ አበባ፣ ብርቱካን ነሽ ሎሚ፣ ትዝታ፣ መሰናበቴ ነው፣ እንደሐገር አይሆንም፣ ውበትም ይረግፋል፣ የከረመ ፍቅር፣ ቀና ብዬ ሣየው የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡